ከወሲባዊ ብዝበዛ፣ጥቃት እና ፆታዊ ትንኮሳ መጠበቅ ስንል  ምን ማለታችን ነው?
ከጥቃት ጥበቃ ሰፋ ተደርጎ ሲተረጎም የልማት ስራ በመስራት እና የሰብዓዊ ድጋፍ በመስጠት ሂደት ውስጥ በሰዎች እና በአካባቢ ላይ ሊደርስ የሚችልን ጉዳት እንዳይደርስ መከላከል ማለት ነው፡፡

የዕርዳታ ፕሮገራሞች (መርሐ-ግብሮች) በአካባቢው ሕዝብ/ማኅበረሰብ ላይ ያልታሰቡ አሉታዊ መዘዞችን ሊያስከትሉ እንደሚችሉ የታወቀ ነው፡፡ በተለይም ወሲባዊ ብዝበዛ፣ ጥቃት እና  ጾታዊ ትንኮሳ በሰፊው የሚታወቅና የተሰነደም (በሰነድ የተመዘገበም) ነው፡፡ አብዛኛዎቹ  የዕርዳታ ድርጅቶች ሠራተኞችና አጋሮቻቸው በጣም ቁርጠኛ እና መርህ ያላቸው ናቸው፡፡ ነገር ግን አንዳንዶቹ በማንኛውም ጊዜ ቢሆን የአካባቢውን ህዝብ በተለይም ተጋላጭ የሆኑ ቡድኖችን  (የማህበረሰብ ክፍሎችን) ሊጎዱ በሚችሉ የጥፋት ተግባራት ሊሰማሩ የሚችሉበት ሁኔታ ሰፊ ነው፡፡ በተመሳሳይ መንገድ፣ ሠራተኞች እና አጋሮች ራሳቸውም በገዛ ባልደረቦቻቸው፣ በሥራ ቦታ ጥቃት ሊያጋጥማቸው ይችላል፡፡

 የመረጃ እና ድጋፍ ማዕከል ሆን ተብሎ ወሲባዊ ብዝበዛ፣ ጥቃት እና ጾታዊ ትንኮሳን በመከላከል እና ተገቢውን ምላሽ በመስጠት ላይ እንዲያተኩር ተደርጎ የተደራጀው እነዚህ መጥፎ ድርጊቶች  በከፍተኛ ደረጃ ተጋላጭ በሆኑ/ አደጋ ውስጥ ባሉ ወገኖች ላይ እጅግ በጣም ከባድ የሆኑ የመብት ጥሰቶችን የሚያስከትሉ በመሆናቸው ነው፡፡ ጥብቅ የጥቃት ጥበቃ ፖሊሲዎች እና የፖሊሲ ትግበራዎች መኖርም ህዝብ በዘርፉ ላይ ያለውን አመኔታ (መተማመን) የሚያጠናክር፣ እንደዚሁም ለዓለም አቀፍ እርዳታና ልማት እየተሰጠ ያለው ድጋፍ ቀጣይነት እንዲኖረው የሚያረጋግጥ ነው።

ትርጓሜዎች
ለማዕከሉ ዓላማ ሲባል የጥቃት ጥበቃ ማለት ወሲባዊ ብዝበዛ፣ጥቃት እናፆታዊ ትንኮሳ እንዳይከሰት ለመከላከል ሊወሰዱ የሚገባቸውን እርምጃዎች ሁሉ መውሰድ፤ በተለይ ለጉዳት ተጋላጭ የሆኑ አዋቂዎች እና ሕፃናትን ጨምሮ ሰዎችን ከጉዳት መጠበቅ እንዲሁም ጉዳት በሚደርስበት ጊዜ ተገቢውን ምላሽ መስጠት ማለት ነው።[1]

ማዕከሉ ከጉዳዩ ጋር ተያያዥነት ላላቸው ፅንሰ ሀሳቦች ትርጓሜ ሲሰጥ የተባባሩት መንግስታት የሚጠቀምባቸውን የሚከተሉትን ዓለም አቀፍ ትርጓሜዎች ይጠቀማል፡፡

ወሲባዊ ብዝበዛ፤ጥቃት እና ፆታዊ ትንኮሳ  እንደሚከተለው ተተርጉመዋል፡-

  • ወሲባዊ ብዝበዛ- ተጋላጭነትን መጠቀሚያ በማድረግ፤ የኃይል ልዩነትን መሠረት በማድረግ ወይም አስቀድሞ የተመሰረተን አመኔታ ለወሲብ ዓላማ እንዲውል አድርጎ መጠቀም ወይም ለመጠቀም ሙከራ ከማድረግ ጋር የተያያዘ ማንኛውንም ድርጊት ያጠቃልላል፡፡ ይህም በሌላ ግለሰብ ላይ በተፈጸመ የወሲብ ብዝበዛ የገንዘብ ፣ የማኅበራዊ ወይም የፖለቲካ ትርፍ ማግኘትን ያካትታል፡፡ በተባበሩት መንግስታት ህጎች መሠረት የወሲብ ንግድን፣የወሲብ ንግድ ድለላን እና ብዝበዛን መሠረት ያደረገ ግንኙነትን ያጠቃልላል።[2]
  • ወሲባዊ ጥቃት- ሀይልን በመጠቀም ወይም ተመጣጣኝነት በሌለበት ሁኔታ ውስጥ ሆኖ ወይም በማስገደድ የግብረ ስጋ ግንኙነት መፈፀም ወይም ለመፈፀም የተደረገ ማስፈራት ነው፡፡ ይህም የወሲብ ጥቃትን (አስገድዶ ለመድፈር መሞከር፣ መሳም/ መነካካት፣ አንድን ሰው በአፍ በኩል ወሲብ እንዲፈጸም/ እንዲነካ ማስገደድ) እንዲሁም አስገድዶ መድፈርን ያጠቃልላል፡፡ በአከባቢው ለአቅመ አዳም/ሔዋን ለመድረስ ወይም ፈቃድን ለመስጠት የተቀመጠው እድሜ ምንም ይሁን ምን በተባበሩት መንግስታት ህጎች መሠረት ዕድሜው/ዋ ከ18 ዓመት በታች ከሆነ ሰው ጋር የሚፈፀም ማንኛውም የወሲብ ድርጊት ወሲባዊ ጥቃት ተደርጎ ይቆጠራል፡፡  ስለልጁ/ቷ ዕድሜ ያለ የተሳሳተ እምነት ወይም ግምት መከላከያ ሆኖ ሊቀርብ አይችልም፡፡ [3]
  • ፆታዊ ትንኮሳ-  የወሲብ ባህሪ ያላቸው ተከታታይነት ባለው መልኩ የሚፈፀሙ ተቀባይነት የሌላቸውና የማይበረታቱ ባህሪያትና ልምምዶች ሲሆኑ እነዚህም በሚከተሉት ሳይወሰኑ ወደወሲብ የሚያመሩ ማሽኮርመሞችን ወይም ጥያቄዎችን፣  ወሲብን ለውለታ ማስፈፀሚያ አድርጎ መጠየቅን እና አፀያፊና ክብረነክ የሆኑ ወይም ይሆናሉ ተብለው የሚገመቱ የወሲብ፤ የቃላት ወይም የአካል ድርጊቶችን ወይም ምልክቶችን ሊያካትቱ ይችላሉ፡፡(4]

የወሲብ ብዝበዛና ጥቃት የተባበሩት መንግስታት ዋና ጸሐፊ መግለጫ  ድንጋጌዎች ጥሰት ነው (ከወሲባዊ ብዝበዛ እና ከወሲባዊ ጥቃት የመጠበቅ ልዩ እርምጃዎች)፤ እንዲሁም “በ(ST/ SGB/2003/13)  ውስጥ በተሰጠው ትርጎም መሠረት ወሲባዊ ብዝበዛ ወይም ወሲባዊ ጥቃት ሆኖ የሚያስቆጥር ስነምግባር ወይም ባህሪ ሆኖ ሲገኝ የወሲብ ባህሪ ያለው ስነምግባር ወይም ባህሪ ነው”፡፡[5]

ከወሲባዊ ብዝበዛ እና ጥቃት መጠበቅ የሚለው ቃል በተባበሩት መንግስታት እና መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች፣ ማህበረሰብ ውስጥ በሰራተኞቻቸው እና በተቀጣሪዎቻቸው አማካኝነት በሰዎች ላይ የሚፈፀሙ ወሲባዊ ብዝበዛዎችን እና ጥቃቶችን ለመከላከል የሚወሰዱ እርምጃዎችን ይገልፃል፡፡[6]

አሁን ላይ በርካታ የእርዳታ ድርጅቶች ወሲባዊ ትንኮሳን እንደአንድ ተያያዥነት ያለው ጭብጥ በመቁጠር ወሲባዊ ብዝበዛና ጥቃት ላይ ብቻ ከማተኮር ይልቅ ወሲባዊ ብዝበዛ፤ ጥቃትና ፆታዊ ትንኮሳን እንዴት መዋጋት እንደሚቻል በብዛት ሲናገሩ ይስተዋላል፡፡ ለዚህም መነሻው ወሲባዊ ብዝበዛ፣ጥቃት እና ወሲባዊ ትንኮሳ እኩልነትን የሚቃረኑ ተመሳሳይነት ያላቸው፣ መዋቅራዊ ችግሮችን የሚጋሩ ስለመሆናቸው ያለው ግንዛቤ እያደገ መምጣቱ ነው፡፡ የጥቃት ጥበቃ ጥሰቶች የተለያዩ መልኮች ሊኖራቸው ይችላል- ለምሳሌ፣ ወሲባዊ ፣ አካላዊ ፣ ስሜታዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና የቃላት ጥቃት።   ምንም እንኳን እነዚህ ችግሮች  በተወሰነ መጠን መፍትሄ ያገኙበት ሁኔታ ቢኖርም ሁሉም ግን የጥቃት ጥበቃ ችግሮች ናቸው፤ መሠረታቸውም የሀይል ልዩነት፤ እና በተለይም ከፆታ ጋር በተያያዘ ያለው  የተዛባ አመለካከት፤ ዘርን፣  ሀይማኖትን፣ የወሲብ ምርጫን፣ አካል ጉዳትን፣ ከኢኮኖሚ እና ከሌሎች ጉዳዮች ጋር የተያያዙ የኑሮ ደረጃዎችንና ማንነትን  መሠረት ያደረጉ ልዩ ጥቅሞች እና መድሎዎች ናቸው፡፡

እነዚህን መሰረታዊ ችግሮች ልዩነቶችን በአግባቡ ማስተናገድ በሚቻልበት መንገድ በመሄድ መፍትሄ ለመስጠት እና ጠንካራ የጥቃት ጥበቃ  ፖሊሲና አሰራርን ተግባራዊ ለማድረግ ተቋማዊ ባህልን የሚፈታ ሁለንተናዊነት ያለው አቀራረብን መቅረፅ ያስፈልጋል፡፡ ይህም እርስ በርስ መከባበርን፤ ሰዎችን ማክበርን እና ሁሉን ማካተትን አጽንኦት ሰጥቶ የሚሰራ ጠንካራ አመራር ይፈልጋል፡፡ በገጹ ላይ የተቀመጡት መረጃዎች ወይም ሰነዶች ወሲባዊ ብዝበዛን፤ ጥቃትንና ትንኮሳን እንዲሁም አጠቃላይ ከጥቃት ጥበቃ ጋር የተያያዙ ችግሮችን ለመፍታት፤ የእርዳታ እና የልማት ስራዎችን በሚሰሩ ድርጅቶች ውስጥ በሙሉ ማንኛውንም ዓይነት ጉዳት የሚከላከል ደህንነቱ የተጠበቀ አካባቢን ለመፍጠር እንደሚጠቅሙ ተስፋ እናደርጋልን፡፡

[1] የመረጃ እና ድጋፍ ማዕከል የጥቃት ጥበቃ ትርጉም

(2) የተባበሩት መንግስታት ( 2017 ) በወሲባዊ ብዝበዛ እና ጥቃት ላይ የቃላት መፍቻ፡፡ ሁለተኛ እትም።  

(3) ዘኒ ከማሁ።

(4) የተባበሩት መንግስታት (2018) በሴቶችና በሴት ሕጻናት ላይ የሚፈፀሙ ማናቸውም ዓይነት ጥሰቶችን ለመከላከልና ለማጥፋት ጥረቶችን ማጠናከር፡ ወሲባዊ ትንኮሳ (A/RES/73/148)፡፡ የተባበሩት መንግስታትጠቅላላ  ጉባኤ     ውሳኔ 

[5]  የተባበሩት መንግስታት (2017)

[6] በጥራት እና በተጠያቂነት ላይ ዋና የሰብአዊነት ደረጃ ጥምረት (CHS Alliance2017)) የወሲባዊ ብዝበዛ፣ጥቃት እና ትንኮሳ መከላከል ትግበራ ፈጣን የማጣቀሻ መጽሐፍ